መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን

መቶ አለቃ አንዳርጌ

ደራሲ መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን በበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ጋይንት አውራጃ ታች ጋይንት ወረዳ አጋጥ መናመስክ በተባለች መንደር ሚያዝያ 21ቀን 1943 ዓ.ም ተወለደ። እናቱ ወ/ሮ አሰገደች አጋዜ እሱን አርግዘው 9ኛ ወራቸው ሲደርስ ለመውለድ ወደእናታቸው ታች ጋይንት ሂደው እዚያ ስለወለዱት ነው እትብቱ አጋጥ መናመሰክ የተቀበረው። በጥቁር ደም መፅሐፉ ላይ ዋና መቸት ሁኖ የምናገኘው መስቀንች የአባቱ እናት አባት (ቅድመ አያቱ) ሀገር ሲሆን አባቱ እናቱን አግብተው እዚያ ይኖሩ ነበር። ሆኖም የመስቀንች ኑሮ ገደላገደል እና ስርጣስርጥ የበዛበት በመሆኑ የዝንጀሮ መንጋ ስለሚንጋጋበት ዘርተው፣ አብቅለው፣ አጭደውና ወቅተው ከጎተራ እስከሚያስገቡ ከዝንጀሮ ጋር መታገል የኑሮቸው አንዱ ፈተና ነበር። በዚህ ምክንያት ወላጆቹ ወደታች ጋይንት ሂደው መኖርን መረጡ። ወዲህ ታች ጋይንት የአባቱ አባት ሀገር ስለሆነ ከእናቱ ጋር ያንድ መንደር ልጆችም ነበሩ። እሱ የ9ኝ ዓመት ልጅ ሲሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መስቀንችን ለቀው ሄዱ። እሱ ግን በጉልምስና ጊዜውም የመስቀንች ትዝታ አልለቀቀውም። ከልጅነቱ ጀምሮ ከዝንጀሮ ቡጫሌዎች ጋር ሲጫዎት በማደጉ የዱር እንስሳት ፍቅር አድሮበት ቀረ። በድርሰት ስራዎቹ መስቀንችን እና የዱር እንስሶቿን ሳይጠቅስ አያልፍም። ጥቁር ደም እና ደም በደም ምስክር ናቸው። 7ኛ እና 8ኛ ክፍሎችን በነፋስ መውጫ ከተማ የተማረ ሲሆን 9ኛ እና 10ኛን ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ጎንደር ፣ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት (በኋላ ፋሲለደስ የተባለው) ተማረ። አንዳርጌ ትምህርቴን ጨርሼ መቼ ስራ ይ እያለ ሲያልም የ1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት ተከሰተ። ደርግ መስከረም 2ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱን ከዙፋናቸው አውርዶ፣በጊዜያዊነት ስም ስልጣኑን እንደጨበጠ፣ ከ10ኛ ክፍል በላይ ያሉ ተማሪዎች በዕድገት በህብረት የሥራና የዕውቀት ዘመቻ ወደገጠር እንዲዘምቱ ሲያውጅ አንዳርጌም ከዘመቱት አንዱ ሆነ። በኋላም በመጣው የእጩ መኮነንት ምልመላ አክስቱ ጎንደርን በኢህአፓ ስጋት እንዲለቅ ከመፈለጋቸው የተነሳ አጥብቀው ለምነውት በእሳቸው ግፊት ተመዝግቦ ለምልመላው አስፈላጊ መመዘኛዎችን አሟልቶ የተሰጡትን ፈተናዎች በማለፍ በእጩ መኮነንነት ሆሎታ ጦር ትምህርት ቤት ገባ። ሥልጠናውን አጠናቆ የሶማሊያ ወረራ እያለ የመጣበት ስለነበር በጥድፊያ ወደ ድሬድዋ ግንባር ተላከ። እንደደረሰም 9ኛ ክፍለ ጦር 25ኛ አየር መቃወሚያ ተመደበ። እሱ እና ባልደረቦቹ የራዳር ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ በሩሲያ እና በኩባ መኮንኖች ተይዞ የነበረውን ያየር መቃወሚያ መዘዣ ጣቢያ እንዲተኩ ተደረገ። አንዳርጌ የጦር መኮንን ነቱን ወድዶት ተቀብሎት ነበር። ጄኔራል ደረጃ ለመድረስም የጋለ ምኞት ነበረው። ሆኖም ግን ይህ ምኞቱ በአንድ መጥፎ አጋጣሚ ምስጥ እንደበለው እንጨት ነኩቶ ቀረ። ምክንያቱ በወቅቱ ወዝ አደር ሊግ እና አብዮታዊ ሰደድ ይባሉ በነበሩ ፖለቲካ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ሽኩቻና እሱ የወዝ አደር ሊግ አባል መሆኑ ነበር። በዚህ የተነሳ ሮጦ ሳይደክም፣ ሠርቶ ሰይጠግብ፣ እስር ቤት ገባ። የሰላ አዕምሮው እንዲላሽቅ ተደረገ። ማዕረጉም በመቶ አለቅነት ተገድቦ ቀረ። ታድያ የ4ዓመት የእሥር ቤት ቆይታው መንፈሱን ወደ ደራሲነት መለሰው። በሥነ ፅሑፍ ውስጥ ራሱን ፈልጎ እንዲያገኝ ዕድል ሰጠው። ቤተክነት ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅትም በቁርጥራጭ ብራናዎች ላይ ይሞነጫጭር ነበር። ደራሲ መቶ አለቃ አንዳርጌ መስፍን ተከታዮቹን ሥራዎች አበርክቷል። • ዳር እስከዳር • ጥቁር ደም • ጥልፍልፍ • ቅሌት • ማኅደረ ደራሲያን • ደም በደም • ሁለገብ አማርኛ ሰዋሰው • ዶክተር ጥንቸል • ተረተረት ለወጣቶች • የቀበሮ ባህታዊ • በሙት መንፈስ ሀገር ሲታመስ • የዝንጀሮች ሰርግ • አባ ዮሎስ

Books by መቶ አለቃ አንዳርጌ :

ቅሌት

ቅሌት

History, Politics, Non Ficition

ሁለገብ አማርኛ ሰዋሰዉ

ሁለገብ አማርኛ ሰዋሰዉ

Communication, Reference, Self Development

ጥቁር ደም

ጥቁር ደም

History, Politics, Ficition

ደም በደም

ደም በደም

Ficition, History, Literature

አባ የሎስ

አባ የሎስ

Non Ficition, Philosophy

አባ የሎስ

አባ የሎስ

Non Ficition, Philosophy