ቅሌት
Summary
ስለደርግ የሰቆቃ አገዛዝ አንድ መጽሐፍ መጻፍ እንዳለብኝ የተገነዘብኩት ላራት ዓመታት በተለያዩ እስር ቤቶች እማቅቅ በነበረበት ወቅት ነበር ፡፡ ‹ጉግማንጉግ › በሚል ርዕስ ረቂቁን የነደፍኩትም ከዚያው እስር ቤት እንዳለሁ ነበር ፡፡ ይሁን እንጅ ደርግ በህይወት እያለ እንደዚህ ያለ መጽሐፍ ማሳተም ስለማይቻል የደርግ ውድቀት እስከ ሚደርስ ድረስ ላይኔ ትኩረትን ፣ ለአእምሮዬ ጭንቀትን የሚፈጥሩትን እየመዘገብኩ ማስቀመጥ ያዝኩኝ ፡፡ ደርግ የፈለገውን ያህል ቢፎክርም በሕዝቡ ዘንዳ ከመወደድና ከመከበር ይልቅ መጠላትንና መዋረድን እያተረፈ መጣ ፡፡ የሕዝብ ድጋፍና ፍቅር በማጣቱም በሥልጣን ላይ አንፈራጦ መቆዬት አልቻለም ፡፡ በመሆኑም እንዳንበሳ ባገሳባት አገር እንደ ዉሻ ጩሆ በያቅጣጫው ፈረጠጠ ፡፡ ጦሩም ፍርክስክሱ ወጣ ፡፡ ከዚህ በኋላ ወያኔ ባሸናፊነት አዲስ አበባ ገባ ፡፡ እኔም ለመጻፍ ያሰብኩትን መጽሐፍ ከደርግ አስከሬን ላይ ለመቋጨት ወሰንኩ ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከም/መቶ አለቃ እስከ ኮሎኔል ማእረግ ድረስ ያላችሁ ጃንሜዳ ከቀድሞው 1ኛ ክፍለ ጦር መምሪያ እንድትከቱ ተብሎ በሬዲዮ ጥሪ በመተላለፉ እኔም አንዱ ማእረግተኛ ስለነበርኩ አብሬ ከተትኩ ፡፡ ይህ አጋጣሚ አዲያዲስ ክስተቶችን እንዳይ ረዳኝ ፡፡ ከጃንሜዳ ወደ ሆለታ መጋዛችን ደግሞ የበለጠ እድሉን አሰፋልኝ ፡፡ ገነት ጦር ት/ቤት ለወር ያህል ስንቆይ የብዙዎቹ መኮንኖች መዝረክረክና ክብር ማጣት ‹ ለካ እንደዚህ ነበርን ? › ብዬ ራሴን እንድ ጠይቅ ተገደድኩኝ ፡፡ የሚንስትሮቹና የጄኔራሎቹ እጅ አሰጣጥም ህሊናዬን አቁስሎት ስለነበር በፊት እየጻፍኩ ካስቀመጥኩት ጋር አያይዠ ለመጻፍ ሳስብ የሚንዛዛብኝ መስሎ ስለታዬኝ የበፊቱን አዘግይቼ ፣ ወቅታዊ የሆነ መጽሐፍ ለመጻፍ አቀድኩኝ ፡፡ የበለጠ የተገፋፋሁት ደግሞ ከሆለታ ወደ ጦላይ ተጋፈን መወሰዳችን ነበር ፡፡ ለሶስት ቀናት ለተሀድሶ ሴሚናር ተብለን ሆለታ ተወስደን ፣ ከዚያ ደግሞ ወደ ጦላይ ጠራርገው በመውሰድ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ ትምህርታዊ ሴሚናር ያሉትን ያጓትቱት ጀመር ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ግን በቋንቋ ፣ በሃይማኖት ፣ በዘርና በጎሳ በመከፋፈል አንድነታችንን አሳጥተው ዉሻ እንደገባበት መንጋ ዝንጀሮ በታተኑን ፡፡ ከዚህ በኋላ በያዳራሾቹ ይታዩ የነበሩት ትርኢቶች እጅግ አድርገው አሳፋሪዎች ነበሩ ፡፡ ለዚህም ነው የመጽሐፌን ርእስ ‹ ቅሌት ! › ብዬ የሰየምኩት ፡፡ ሁሉን ነገር ጨርሸ ለማሳተም ላይ ታች ስሯሯጥ በሌሊት ከመኗሪያ ቤቴ ባፋኞች ታፈኜ ስወሰድ ለረጅም ጊዜ እየጻፍኩ ያጠራቀምኳቸው ሁሉ ፣ ይኸው ራሱ ቅሌት ጭምር ከኔው ጋር ለእስር ተዳረጉ ፡፡ ከእስር ቤት እስር ቤት ስዘዋወር ቆይቼ ካንድ ዓመት የእስር ጊዜ በኋላ እኔ ስፈታ ጽሑፎቼ ግን ከኔ የከፉ ወንጀለኞች ሆነውም እንደሆነ አላውቅም በዚያው ሰጥመው ቀሩ ፡፡ ላሳሪዎቼ ከመፈታቴ በፊትም ሆነ ከተፈታሁ በኋላ ጽሑፎቼን እንዲመልሱልኝ አመልክቼ ሳይሳካልኝ ቀርቷል ፡፡ ቅሌትን ግን ከእስር ቤት እንደ ወጣሁ ያለና የጠፋ ንብረቴን ሳፈላልግ ረቂቅ የነደፍኩበትን ካልባሌ ቦታ ተወሽቆ በማግኜቴ እንደ ገና ጀምሬ ከግብ ላደርሰው ችያለሁ ፡፡ እንግዲህ ዋና አዓላማዬ አንዱን ክቤ ሌላውን ለማዋረድ ወይንም ያልተሠራና ያልተደረገ ነገር ጽፌ ስም ለማጥፋት አይደለም ፡፡ ከኛ ውድቀት የነገው ትውልድ ትምህርት እንዲያገኝበት ለማድረግ ነው ፡፡ በተለይም ከወያኔዎች እጅ ላይ ከወደቅን በኋላ ለጥቂት ጊዜ ራሳችንን መቆጣጠር አቅቶን እጅግ አሳፋሪ ድርጊቶችን ሠርተናል ፡፡ ይህ መቼም ቢሆን በይቅርታ ሊታለፍ የሚገባው ተግባር አይደለም ፡፡ የነገው ትውልድ ሊማርበት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ባይነኝ ፡፡ በርግጥ ቆፍጣና መኮንኖች የነበሩ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን ተበሻቅጠው አበሻቅጠውናል ፡፡ አገሪቱም የሞተችውና የተዋረደችው ገና ከማለዳው ሀላፊነትን መሸከም በማይችሉ መዳፍ ላይ የወደቀች እለት ነበር ፡፡ ደርግ ኢትዮጵያን አዋረወዷታል ! ገሎ ለቀባሪዎች አሳልፎ አስረክቧታል !! በወያኔዎች አስተናናቂነት አጋላጭና ተጋላጭ ጦላይ ላይ ሲተናነቁ ማየት የሚያሳፍርም ፣ የሚያሳዝንም ፣ የሚያስቅም ነበር ፡፡ የበደለና የተበደለ ቢተናነቁ ኖሮ ባልከፋ ነበር ፡፡ ይናከሱ የነበሩት ትንሹ ዘራፊና ትልቁ ዘራፊ ነበሩ ፡፡ እንግዲህ ወጣቱ ትውልድ ከእንዲህ ዓይነቱ ውርደት ምን ይማራል ? ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው ፡፡ በራሱ የተማመነ ኩሩ ወጣት ትውልድ ለማፍራት መራር ትግል የሚጠይቅ መሆኑን አበክሮ መንገር ያስፈልጋል ፡፡ ኢትዮጵያንም እንደ ጥንቷ የኮራችና የታፈረች ሀገር ለማድረግ የሚቻለው ኩሩ ወጣቶችን ማፍራት ሲቻል ብቻ ነው ፡፡ አለበለዚያ የጎሳ ሆያሆዬ የትም አያደርሰንም ፡፡ ይህን የጎሳ ሆያሆዬ የሚሹት ደግሞ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የቤት ሥራ የተቀበሉ ጨካኞች ብቻ ናቸው ፡፡ ጎሰኞች መቼም ቢሆን ኢትዮጵያን አንድነት አይፈልጉም ፡፡ ተልእኳቸው ነውና !! በተረፈ በህይወት ከእስር ቤት ወጥቼ ቅሌትን ለቁም ነገር በማብቃቴ ታላቅ እፎይታ አግኝቻለሁ ፡፡ እንግዲህ ወደ ዋናው ምንባብ የምታደርስ ግጥም ጣል አድርጌ ልሰናበት ፡፡ ግብሩንም ፣ ታክሱንም ሁሉን ሲምሩት አሥራትን ብቻ ነው አንተውም!!