መክት ፋንቱ (መምህር)

በ1968 ዓም የካቲት 27 ነው የተወለደው፡፡ እትብቱ የተቀበረው ተጂ የምትባል አነስተኛ ከተማ ቢሆንም ከሦስት ወር በገፋ ተጂ ላይ አልኖረባትም፡፡ በመንግስት ሥራ ላይ የነበረሩ ቤተሰቦቹ ወደ ወልቂጤ ኑሯቸውን ሲያደርጉ በአንቀልባ ታዝሎ ወልቂጤ ገባ፡፡ ለአቅመ ትምህርት እንደደረሰ ከነ የኔታ ነው ሀ ግእዝ ሁ ካዕብ እያለ ነገረ ትምርትን የጀመረው፡፡ ከዚያም አንደኛ ደረጃውን ራስ ዘሥላሴ በሚባለው እድሜ ጠገቡ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ወልቂጤ፤ ጎሮ በሚባለው ትምህርት ቤት ቢጀምርም ለትምህርት ልዩ ቦታ የሚሰጡት ቤተሰቦቹ ለተሻለ ትምህርት አቃቂ አድቬንቲስት አዳሪ ትምህት ቤት ላኩት፡፡ እንግዲህ ነገረ ሃይማኖትንም ሆነ ስነ ጽሑፍን ማጣጣም የጀመረው በዚህ እድሜ ነው፡፡ እዚያው የአሁኑ ሚካኤል ታምሬ መድረክን የረገጠበትን ፍቅር እስከወዲያኛው የተሰኘ ቲያትር ጽፎና አዘጋጅቶ እስከ ሶደሬ ድረስ ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡ በሃይማኖት ረገድም የኦርቶዶክስን ሃይማት አጥብቆ በማስተማሩ ከአድቬንቲስት አካላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከትምህርት ቤቱ እንዲባረር የተደረገ ሲሆን እሱም በደስታ ተቀብሎት ወልቂጤ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጥሏል፡፡ ለስነ ጽሑፉም ቢሆን የተወዳጃቸው ሰዎች ቀላል የሊባሉ አልነበሩም፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ደግሞ ዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ነው፡፡ ይሁንና በሃይማቱ እየገፋበት መምጣቱ ትምህርቱን በይበልጥ ለማዳበር ገዳም ገብቶ ሥነ ጽሑፉን ርግፍ አድርጎ ትቶት ነበር፡፡ ከተወሰኑ አመታትም በኋላ አዲስ አባባ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ የነገረ መለኮት ትምህርቱን በዲግሪ መርኀ ግብር አጠናቋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮችም ላይ ያለውን እውቀት ለማሳደግ የተለያዩ ትምህርቶችን ቀስሟል፡፡ በንባብም አዳብሯል፡፡ አሁን በዋናነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እያገለገለ ሲገኝ ከዋናው ሥራ ባልተናነሰ የተላያዩ መጻሕፍትን በመጽሐፍ ላይ ይገኛል፡፡