
ጳዝዮን
Summary
ጳዝዮን የከበረ ማዕድን ሲሆን እንደ ዕንቁና ወርቅ ያንጸባርቃል። ላወቀው እንጂ ክቡርነቱ ላላወቀው የትብያ ያህል ነው። ተራ አልባሌ። 'ሰው'ነት ጳዝዮን ነው። ጊዜና አካባቢ ከነ ሙላቷ ጳዝዮን ናቸው።ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል እና መሰል አኩሪ እሴቶች ጳዝዮኖች ናቸው። ለራስህ በምትሰጠው ሚዛን የምትገመት አንተም ጳዝዮን ነህ። እነዚህ ሁሉ አዋቂ አክባሪና ተጠቃሚ ይሻሉ። ካላገኙ ተራ ነገር ሆነው ያልፋሉ። መጽሐፉ ውስጥ በጳዝዮን ሊመሰሉ የሚችሉ መልካም ባህርያት፣ ህልም፣ እውቀትና ዕምቅ ክህሎት ትርጉም አግኝተው ለሌላው ተርፈው ሲገኙ፤ ትርጉም ጊዜና ቦታ ተነፍጓቸው ቁጭት ወይም የእግር እሳት ሆነው ተስተውለዋል። በመልካም ማንነታቸው የሚወደዱ ገጸ ባህርያቱ ቅርብ ሆነው የእውነት በእውነት ሊዋደጇቸው የሚናፈቁ ናቸው። እንደ አባት ይከበራሉ፣ እንደ ወንድም ያስመካሉ፣ እንደ እህት ይናፍቃሉ፣ እንደ ጓደኛ ለምክርና ጫወታ ይፈለጋሉ። የሚጠቅሙ ጳዝዮኖች ይሆናሉ። ከርሰ ምድር ቆፍረው ትብያ አራግፈው አንጸባራቂ ጳዝዮን ያገኙ እድለኛ ያደርጋሉ። አካባቢአቸውን አክብረው የከበሩ ጳዝዮኖች የሚተዋወቁበት ሲሆን ራስን አስመርምረው ከነሱ እንደ አንዱ ለመሆን የሚያስመኙ፤ የሚያስወስኑም፤ ለጳዝዮንነት ራስን የሚያሳጩ ናቸው። በአንጻሩ ጳዝዮን ትርጉም አጥቶ እንደ ትብያ መረጋገጫ ሲሆን ያስቆጫል። ያንገበግባል። ያበሳጫል።ለጥቅም እንጂ ለጥፋት የተፈጠረ ምንም የለምና ያስቆጨ፣ ያንገበገበ፣ ያበሳጨ ቆም ብሎ ነገን ከነ በረከቷ በማመን የጳዝዮን አካል በመሆን ክብርና ሞገስ ያጎናጽፋል።