እንዳለጌታ ከበደ
ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍና የፎክሎር ተመራማሪ፡፡ እንዳለጌታ ከበደ፣ ውልደቱም እድገቱም ወልቂጤ ነው፡፡ በወልቂጤ ከተማ ውስጥ፣ የመጀመርያና የመለስተኛ ደረጃ ትምሕርቱን በራስ ዘሥላሴ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ደግሞ በጎሮ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ያገባደደ ሲሆን፣ በ1990ዎቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ዲፕሎማ ከዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፣ በቴአትር ጥበባት ትምሕርት ባችለር ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በዚሁ ዩኒቨርስቲ በሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምሕርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪውን የያዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በፎክሎር የትምሕርት ዘርፍ የሦስተኛ ዲግሪ ትምሕርቱን በማገባደድ ላይ ይገኛል፡፡ እንዳለጌታ ወደ ሥነ ጽሑፍ ዓለም የገባው በልጅነቱ ሲሆን፣ በትምሕርት ቤት መድረኮች ራሱን ግጥሞችንና ድራማዎችን በማቅረብ ካለማመደ በኋላ፣ በ‹‹አዲስ አድማስ›› ሳምንታዊ ጋዜጣ አጫጭር ትረካዎቹንና መጣጥፎቹን በማስነበብ ከአንባብያን ጋር ለመተዋወቅ በቅቷል፡፡ እስካሁን ድረስ፣ ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን ከሠራቸው፣ በአርታኢነት ከተሳተፈባቸው መጻሕፍት ሌላ (‹‹ደቦ - ቅጽ 1›› እና ‹‹ደቦ - ቅጽ 2››ን ልብ ይሏል) በግሉ፣ ከ1996 – 2013 ባሉት ዓመታት፣ አስራ ሦስት መጻሕፍትን ያስነበበ ትጉ ደራሲ ሲሆን፣ ሥራዎቹም በአራት ይመደባሉ፡፡ እነዚህም (1) አጫጭር ትረካዎች (‹‹ከጥቁር ሰማይ ስር›› - 1996፣ ‹‹የመኝታ ቤት ምስጢሮች›› - 2000፣ ‹‹ጽላሎት›› - 2004፣ ‹‹መክሊት›› - 2012) (2) ረጃጅም ልቦለዶች (‹‹ዛጎል›› - 1998፣ ‹‹ደርሶ መልስ›› - 2001፣ ‹‹እምቢታ›› - 2006፣ ‹‹ምሳሌ›› - 2010) (3) ኢ - ልቦለድ ሥራዎች (‹‹ኬር ሻዶ›› - 2001፣ ‹‹ማዕቀብ›› - 2006፣ ‹‹በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ› ›- 2006 እና ‹‹ያልተቀበልናቸው›› - 2009) (4) የግጥም ስብስቦች (‹‹ልብ ሲበርደው›› - 2001) ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል፣ በ1860ዎቹ በጉራጌ ምድር ተወልዳ፣ የሴቶች መብት እንዲከበር ‹አብዮት› ስላስነሳችው፣ ስለየቃቄ ወርድወት ታሪክ የሚተርከው፣ ፎክሎራዊና ታሪካዊ ልቦለዱ ‹‹እምቢታ›› የተሠኘ ሥራው፣ በዕውቁ ተርጓሚና ደራሲ በሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያም ‹‹THE DEFIANT›› በሚል ርዕስ ተተርጉሟል፡፡ በቅርቡ ለኅትመት እንደሚበቃም ይገመታል፡፡ ይህ ‹‹እምቢታ›› የተሰኘው መጽሐፍ፣ እናት ባንክ በባለታሪኳ በየቃቄ ወርድወት ስም ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲከፍት ምክንያት ሲሆነው፣ የመጽሐፉ ታትሞ መውጣት፣ የባለታሪኳን ሕይወትና የወጣችበት ማኅበረሰብ በኪናዊ ሥራዎች እንዲገለጽ ገፊ ምክንያት ሆኗል፤ በተለይ በቴአትሮችና በባህላዊ ዘፈኖች፡፡ በሌላ በኩል፣ ‹‹ማዕቀብ››ና ‹‹በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ›› የኢትዮጵያ ደራስያን ለሙያቸውና ለሀገራቸው ብለው ስለከፈሉት መስዋዕትነት፣ በሳንሱር የተነሳ ተዳፍነው ስለቀሩ ሃሳቦችና እንደዋዛ ወጥተው ስለቀሩና ለሙያቸው ሕይወታቸውንም ጭምር ስለከፈሉ እምር ደራስያን ሲተርኩ፣ ‹‹ደርሶ መልስ››፣ ‹‹ዛጎል››ና ‹‹ምሳሌ›› ደግሞ በተለየ የአተራረክ ስልታቸውና የቋንቋ ለዛቸው፣ የአጫጭር ትረካ መጻሕፍቱም በአጻጻፍ ቴክኒካቸውና የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሕይወት በመፈተሻቸው መልካም ስም አትርፈውለታል፡፡ እንዳለጌታ፣ በወልቂጤ ከተማ፣ በ1989 ዓ.ም፣ ‹‹ተስፋ መጻሕፍት ቤት›› የተሰኘ ማዕከል ከፍቶ፣ ለሃያ አራት ሰዓት ሃያ አምስት ሳንቲም እያስከፈለ፣ የማንበቢያ ቦታ እያመቻቸ፣ አንጋፋ ደራስያን ከከተማው ነዋሪዎችና አድናቂዎቻቸው ጋር እንዲገናኝ እያደረገ፣ የሥነ ጽሑፍ ውድድር እያዘጋጀ፣ በርካቶችን በንባብ አንጾና በሚከተለው የጥበብ ,ፈለግ ተከታይ ማፍራት የቻለ ደራሲ ነው፡፡ ከመጻሕፍት ቤቱ በተጨማሪም፣ ከእህት ወንድሞቹ ጋር በመሆን፣ በእናታቸው ስም፣ እ.ና.ት (እልፍነሽ ናጂ ትምሕርት አጋዥ በጎ አድራጎት ድርጅት) የተሰኘ ድርጅት በ2012 ዓ.ም ጀምሮ በመክፈት፣ የመማር ዕድል ላላገኙ ለሃያ አምስት ተማሪዎች እድሉን አመቻችቶላቸዋል፡፡ ድርጅቱም በቤተሰቡ አባላት የሚደጎም ሲሆን፣ ተማሪዎቹ በየቀኑ ምሳቸውን የሚበሉበት፣ የደብተር ወጪያቸው የሚሸፈንበትና በአቅም ማጣት ምክንያት ከትምሕርታቸው የማያስተጓሉበትን አቅም በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ በሥነ ጽሑፍና በፎክሎር ተመራማሪዎች ዘንድ ተተንትነዋል፡፡ ከመጻሕፍቱ ውጪም፣ በጥናትና ምርምር መጽሔቶችና የጥናት መድረኮች ‹ወረቀቶች›ን በማቅረብ፣ በጋዜጦችና መጽሔቶችም በዐምደኝነት የተሳተፈ ሲሆን፣ ከእነዚህ የኅትመት ውጤቶች መካከል ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣና መጽሔት፣ ‹‹ፋክት›› እንዲሁም ‹ለዛ› መጽሔት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ‹‹ይሉኝታ›› የተሰኘውን ልቦለዳዊ ፊልም ድርሰት ከቢኒያም ወርቁ ጋር ጽፎት፣ በሚካኤል ሚሊዮን ዳይሬክተርነት በግሩም ኤርሚያስና ሜሮን ጌትነት መሪ ተዋናይነት ለዕይታ የበቃ ሲሆን፣ EBS ቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረና ‹‹አርአያ ሰብ›› በተሰኘው ሳምንታዊ ፕሮግራም ላይም፣ ከሰላሳ በላይ ዕውቅ የኢትዮጵያውያን መሪዎች፣ የሀገር ስም አስጠሪዎች፣ የአርበኞችና አትሌቶች ሕይወት የሚተርኩ ለዘጋቢ ፊልሙ የሚሆኑ ጽሑፎችን አበርክቷል፡፡ እንዳለጌታ ለሥነ ጽሑፍና ለንብብ መዳበር ባበረከተው፣ በወጣቶችና በልጆች ሥነ-ምግባራዊ ዕድገት ላይ ባበረከተው አስተዋጽዖ ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና የምስክር ወረቆቶችን ከተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት የተቀበለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል፣ በ2005 ዓ.ም ያገኘው ‹‹ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት›› እጅጉን ይታወቃል፡፡ እንዳለጌታ፣ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባነት፣ በዚሁ ዩኒቨርስቲ በተቋቋመውና በክቡር ደራሲ ከበደ ሚካኤል ስም በተሰየመው የባሕል ማዕከል ውስጥ በዳይሬክተርነት፣ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በዋና ጸሐፊነት (ከ1997-2005 ድረስ፣ በነጻ) እንዲሁም፣ በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ውስጥ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ውስጥ በመስራችነትና በዳይሬክተርነት ለአራት ተከታታይ ዓመታት አገልግሏል፡፡ እንዳለጌታ በአሁኑ ወቅት፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በፈረንሳይ ለጋሲዮን ሲያደርገው ቆይቶ በሁኔታዎች አለመመቻቸት አቋርጦት የነበረውን ተግባር በማዘመን፣ የተለያዩ ጥበባት የሚከወኑበት፣ ከያንያን ራሳቸውን የሚገልጹበት ‹‹ዛጎል ቤተ ጥበባት›› የተሠኘ ድርጅት ከፍቶ፣ በሥሩም ‹‹ቡክ ባንክ›› በማቋቋም ንባብና አንባቢ በመላ ኢትዮጵያ እንዲደረጅ፣ መጻሕፍት ቤት እንዲስፋፋና መጠየቅና ማሰላሰል የሚችል ዜጋ በመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ሲገኝ፣ ኑሮውም ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ ነው - ከባለቤቱ እሌኒ መስፍንና ከልጆቹ ኤማንዳ፣ አብይካብና ኢዮአስ እንዳለጌታ ጋር፡፡