እምቢታ
Summary
ይህ ‹እምቢታ› የተሰኘው የእንዳለጌታ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታሪክ የሴት ልጅን መብት ለማስከበር በማሰብ፣ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት በሰባት ቤት ጉራጌ ውስጥ ይህንኑ ጥያቄ በማስነሳት ትታወቅ ስለነበረችና የቃቄ ወርድወት ስለተሰኘች ሴት የሚተርክ፣ ፎክሎራዊና ታሪካዊ ልቦለድ ነው፡፡ ልቦለዱ፣ ሰው ሃይማኖቱን፣ ነባር አቋሙን፣ ባህሉን ላለመተው ስለሚያደርገው ተጋድሎና እምቢተኝነት ከመተረኩም በተጨማሪ፣ ተለያይቶ ከመኖር ይልቅ አንድነት እንዴት ለአንዲት አገር ጠቃሚ መሆኑን በተለያዩ ትዕምርቶች ማሳያነት ያሳያል፡፡ ይህ መጽሐፍ ከታተመ በኋላ፣ የማኅበረሰቡ ተወላጆች ለባለታሪኳ አዳዲስ ዘፈኖችን ደርሰዋል፡፡ እናት ባንክም በስሟ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲከፍት ገፊ ምክንያት ሆኖታል፡፡ ሃያሲና ገጣሚ ደረጀ በላይነህ፣ ይህ መጽሐፍ ታትሞ በወጣ ሰሞን፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ‹‹ወርድወት በጉራጌ ምድር የበቀለች የኢትዮጵያ ሴቶች የተስፋ ምንጭና ሰንደቅ ናት/..../ እንደበረሃ ንፋስ እየተሸረከረች ሰማይ የደረሰ ምሰሶ ሰርታ የሀገሬውን ድንኳነው የናጠችው ሴት፣ እስካሁን በኢትዮጵያውያን ደራስያን ከተሳሉት ገጸባህርያት በተለይ ታላቅ ሆና ተፈጥራለች፡፡ ከተዳፈነችበት የታሪክ ዓመድ እፍፍ ብሎና ቆስቁሶ ያስነሳት ደራሲ፣ በዚህ ታላቅ ጭብጥ የተነሳ ሊመሰገን ይገባዋል ባይ ነኝ›› ብሎ ነበር፡፡