ከፈለኝ ዘለለው
መምህር ፣ የሕይወት ክህሎት አሰልጣኝ እና ደራሲ ከፈለኝ ዘለለው የ "ጥበብ ከተማ" ተብላ በምትታወቀው "ቀጨኔ" ውስጥ በ 1969 ዓ.ም ተወለደ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በ "ቀጨኔ ደብረ - ሰላም" እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን "እቴጌ መነን" ት/ቤት አጠናቋል። ከጥበብ ጋር የተገናኘ ትምህርቱን ደግሞ ብዙ ስመ - ጥር ጥበበኞችን ባፈለቀው "ሆሊ ላንድ አርት አካዳሚ" ውስጥ ተምሮ "በአፃፃፍ ፣ በትወና እና በመድረክ ዝግጅት" ተመርቋል። ከጥበብ ጋር ባልተገናኙና አካዳሚክ በሆኑ በሌሎች በርካታ የትምህርት ዘርፎችም ከተለያዩ ተቋማት የተለያዩ ኮርሶችን ወስዷል፡፡ መምህርና ደራሲ ከፈለኝ ዘለለው የበርካቶችን አዕምሮ በገንቢ ሀሳቦች በማነፅ የሚታወቀው የ "ሐዋዝ በጎ ሀሳብ ማጋሪያ ማዕድ" ዋና አዘጋጅ መሆኑም ይታወቃል። በተለያዩ "የበጎ አድራጎት ማሕበራት" ውስጥም በመሪነት በማገልገል ለበጎነት ኖሮ ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡ በ 1995 ዓ.ም "የሻማ ብርሃን ፩" ፤ በ 2004 ዓ.ም "አገልፋኖ" ፤ በ 2007 ዓ.ም "አሞዛ" ፤ በ 2014 ዓ.ም መጀመሪያ "ሐዋዝ" እና በ 2014 ዓ.ም መጨረሻ "የሻማ ብርሃን ፪" የተሰኙ አምስት አንቂና አትጊ መፅሐፍትን አሳትሞ ለአንባብያን አበርክቷል። በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮችም ላይ ተጋብዞ የጥበብ ሥራዎቹንና የሕይወት ተሞክሮውን አካፍሏል፡፡ ደራሲው "ለመስጠት ኑር (LIVE TO GIVE)" በሚል ቀና የሕይወት መርሁ ለአያሌ ጀማሪ ጥበበኞች የመድረክ ዕድሎችን ፈጥሯል። ለእውቅናም አብቅቷል፡፡ ሕፃናትንም በቅን ስነ - ምግባር በማነፅና ከቡቃያነት ዕድሜአቸው ጀምሮ "በመልካም ትውልድነት እንዲያድጉ" አቅዶ በመስራት ረብ ያለው ውጤትን አስመዝግቧል፡፡ ከአስር ዓመታት በላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት ያገለገለው ደራሲ ከፈለኝ ለተለያዩ መንግሰታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሰራተኞች እንዲሁም ለአንደኛ ፣ ለሁለተኛና ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት እያነቃ ልዩነትን የፈጠረ ፀሐፊ ነው፡፡