ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ

ዶክተር በድሉ

በድሉ ዋቅጅራ ኢትዮጵያ ካሏት ታላላቅ ገጣምያንና ደራስያን መካከል አንዱ ነው፡፡ አምስት የግጥም ስብስቦችን አሳትሟል፡፡ ‹‹ሀገር ማለት የእኔ ልጅ›› የሚለው ግጥሙ እንደብሄራዊ መዝሙር የሚቆጠር ነው፡፡ በድሉ ከግጥም በተጨማሪ የአጫችር ተውኔቶች፣ የአጫጭርና የረዣዥም ልቦለዶች ደራሲም ነው፡፡ የመጀመሪያ ረዥም ልቦለዱ፣ ‹‹ችካል እና እርምጃ›› እንደታተመ ሰፊ ተነባቢነትን ያገኘ ተወዳጅ ስራው ነው፡፡ የግጥም ስራዎቹ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉመው እንደ "Modern Poetry in Translation" እና "PN:Review" ባሉ የተለያዩ አለምአቀፍ ህትመቶች ውስጥ ከመውጣታቸውም በላይ፣ የመጀመሪያ በሆነው "Songs We Learn from Trees" በተባለ በእንግሊዘኛ በተተረጎሙ የአማርኛ ግጥሞች ስብስብ (anthology of Ethiopian Amharic poetry in English) ተካተዋል፡፡ ገጣሚና ደራሲ በድሉ ዋቅጅራ (ፒኤችዲ) ከስነጽሁፍ ስራዎቹ በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ በሚያቀርባቸው ፖለቲካዊና ማህበረ-ባህላዊ መጣጥፎቹም ይታወቃል፡፡ በድሉ ዋቅጅራ (Ph.D.) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋና ስነጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ በቋንቋ ማስተማር ሁለተኛ (M.A) ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኖርዌይ ሀገር ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስነልሳንን (General Linguistics) ለሁለተኛ ዲግሪ (M.Phil.) እና ለሶስተኛ ዲግሪ (Ph.D.) አጥንቷል፡፡ የስነልሳን ጥናቱ የሴም ቋንቋዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በተለይ በክስታንኛ ቋንቋ ስነምእላድና ሰዋስው (Morpho - Syntax) በርካታ ጥናቶችን አድርጓል፡፡ ከነዚህም መካከል፣ "Verbal extensions and argument structure in Kistaninya" (2000) እና "Morphology and verb construction types of Kistaniniya." (2010) በዘርፉ ምሁራን ታዋቂነትን ያተረፈባቸው ናቸው፡፡ በአርትኦትና በጸሀፊነት የተሳተፈበት፣ በቅርቡ ተጠናቅቆ በአሁኑ ወቅት በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ለህትመት በሂደት ላይ የሚገኘው፣ "Oxford Hand book of Ethiopian Languages" የተባለው መጽሀፍ በኢትዮጵያ የቋንቋና ስነልሳን ጥናት ያለውን የመረጃ ክፍተት ይሞላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሰላሳ አመታት በፊት፣ በ1983 አ.ም. መምህርነትን በሁለተኛ ደረጃ ‹‹ሀ›› የጀመረው በድሉ፣ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነጽኁፍ መምህር ነው፡፡

Books by ዶክተር በድሉ:

ጠርዝ ላይ

ጠርዝ ላይ

Non Fiction, History, Politics

የማይጻፍ ገድል

የማይጻፍ ገድል

Non Fiction, History

የራስ ምስል

የራስ ምስል

Poetry, Literature