ይበልጣል አድማስ
ይበልጣል አድማስ መኮነን ይባላል የተወለደው በደቡብ ጎንደር እስቴ መካነ-ኢየሱስ ከተማ በ1982ዓ/ም ነው። የፅሁፍ ዝንባሌው የጀመረው በልጅነቱ ነው። የፅሑፍ ምንነቱን አያውቅም ነበር፤ ትምህርት ቤትም ሆነ ከየኔታ ገበታ አልተቀመጠም። ነገር ግን ማታ ማታ ከሣር ቤታቸው ከምድጃው ውስጥ በሚነዳው እሳት ዳር ከትልቅ ወንድሙ ጋር ተቀምጦ እናታቸው ቡና እያፈላች ሁሌም በደርግ ዘመነ መንግሥት ስለደረሰባት ሥዕላዊ ትረካ ትትርክላቸው ነበር። በልጅነት እዕምሮው የምትተርክላቸው ትረካ ሁሌም ስለነበር ቀስ በቀስ ከዕድሜው ጋር እየጎለበተ ሄደ። በሰባት ዓመቱ ወደ ቄስ ትምህርት ሄደ፤ በዘጠኝ ዓመቱ ደሞ በመካነ ኢየሱስ ከተማ ማቢ አቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባ። እስከ ሥምንተኛ ክፍል ተምሯል። ከዚያም ከዘጠኝ እስከ እሥራ ሁለተኛ ክፍል ደሞ በመካነ ኢየሱስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ ወደ ዩኒቨርስቲ ማለፊያ ነጥብ አምጥቶ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ተምሯል። ከተወለደበት ሠፈር ራቅ ብዬ ኢትዮጵያን የሚያይበት ዕድል በመፈጠሩ ደስታው ጥሩ ነበር። ሚዛን ቴፒ ዪኒቨርስቲ በኢሌክትሪካል ምህንድስና የመጀመሪያ ድግሪውን ይዟል። መፅሀፍ ውድ ጓደኛው የሆነው አስረኛ ክፍል ሲደርስ ነው። የሚያገኘውን ሁሉ ያነብ ነበር፤ ዪኒቨርስቲ ሲገባ የበለጠ መፅሀፍ ያገኝ ነበር። ጓድኞቹም ከተለያየ ቦታ ስለሚመጡ ያመጡለት ነበር። ኢትዮጵያን በደንብ አይቶበታል፤ ውብ ጓደኞችም ፈጥሮበታል። አሁን በመንግሥት ሥራ ውስጥ እየሠራ ይገኛል። ለሕዝብ ኹለት መጽሐፍትን አቅርቧል፤ የመጀመሪያው በ2012ዓ/ም የባህል ቋጠሮ ሲሆን ኹለተኛው ደሞ የዕርግብ እሾህ የሚል በ2014ዓ/ም ተደራሽ አድርጓል።