ማሩ እንዳለ ባልቻ

ማሩ እንዳለ ባልቻ አቃቂ መሃል ከተማ በወርሃ ጥር 1963 ዓ.ም እግዚአብሔር መልካም ፍቃዱ ሆኖ ወደዚህች ምድር መጣ ፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለያየ ሁኔታ ይሳተፍ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዓፄ ቴዎድሮስ የሕዝብ ትምህርት ቤትና በፊታውራሪ አባይነህ መተኪያ ትምህርት ቤት ተምሮ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የግጥምና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን አጥብቆ የጀመረው በዚሁ ትምርት ቤት ነበር፡፡ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አቃቂ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲከታተል በትምህርት ቤቱ በተለያዩ ክበባት በተለይ በጋዜጠኞች ክበብ በሚኒ ሚዲያ ጋዜጠኝነት ትምህርት ቤቱን እስኪለቅ ድረስ ተሳታፊ ነበር በዚሁ ትምህርት ቤት ራሱ የደረሰውን እና ሌሎች ልጆች በጻፏቸው ድራማውች ላይ ተሳትፏል፡፡ ከትምህርት ቤት ከወጣ በኋላ ባቋቋሙት የቲያትር ክበብ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል። በተጨማሪም ሙያውን ለማሻሻል የተለያዩ የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች በመማር ዲፐሎማና ሠርተፊኬቶችን ይዟል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው የኪነ ጥበብ ፍቅር አሁን እስካለበት ግዜ ድረስ ተከትሎት በተለያዩ ፊልሞች እንደ ሳልሳዊ ፣ አድናት ፣ አታመልጪኝም ፣ አልበም ፣ አዱኛ ፣ የነገን አልወልድም ፣ ትሩፋን ፣ እና ሌሎችም ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ በቴሌቪዥን ሥራዎች ላይ ደግሞ ችሎት ላይ የተለያየ ርዕስ ያላቸው ድራማዎች ላይ ተሳትፏል ፣ ትርታ ፣ የዕግር እሳት ፣ አየር በአየር ፣ አደይ እና ሌሎችም ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ እንዲሁም የተለያዩ የድርጅት ማስታወቂያዎች ላይ በመሳተፍ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ በሥራው ውስጥ ቆይቷል ፤ ከዚያ በተጓዳኝ በነዚሁ ተመሳሳይ ዓመታት የግጥም ሥራዎች በመሥራት በ2015 ዓ.ም ሳቅሽ ይናገራል በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን የመጀመሪያ የግጥም መድብል ለሕዝብ አቅርቧል፡፡ ይህንኑ የግጥም መድብልና የተረሳች ሃገር በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሁለተኛውን ቅጽ በድምጽ እና በሶፍት ኮፒ በአፍሮሪድ መተግበሪያ ለህዝብ አቅርቧል ፡፡ በቀጣይነት በቅርቡ በተሳተፈባቸው በተለያዩ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችና ፊልሞች ላይ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ መተግበሪያ ወጥ ልብ ወለዶችን በድምጽና በሶፍት ኮፒ ለማቅረብ በዝግችት ላይ ይገኛል ፡፡