ቃለጽድቅ በላይነህ
ቃለጽድቅ በላይነህ በ1986 ዓም በምዕራብ ጎጃም ዞን በፍኖተ ሰላም ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው። እናቱ ይመኙሻል በየነ እና አቶ በላይነህ አገናኘው ያወጡለት ስም "ደመወዝ" የሚል ነው። በዚሁ ስሙ ይታወቃል። የአንደኛ ፥ የሁለተኛ ደረጃና የመሠናዶ ትምህርት ቤት ቆይታውን እዚያው ፍኖተ ሰላም እስከ 2004 ዓ ም ተምሮ አጠናቋል። በዚህ የ 12 ዓመታት የትምህርት ቆይታው ለትምህርቱ ከሚሰጠው ትኩረት ጎን ለጎን የጥበብ ሥራዎች ይስቡት ስለነበር በየጊዜው የሚያገኛቸውን ልምዶቹን ለማዳበር እንደ ስዕል ግጥምና አጫጭር ድርሰቶችን እያዘጋጀ ለጓደኞቹ ለማሳየት ይሞክር ነበር። ከጥበቡ ዘርፍ በተጨማሪ የልጅነት ልቡን የመርከብ ካፕቴን የመሆን ህልምም ይወዘውዛት ነበር። በዚህ ሁሉ መካከል የቤተክርስቲያን ትምህርት ለመማርና አዳዲስ የማያውቃቸው ነገሮችን ለማወቅና ለመሳተፍ መሞከሩ አልቀረም። ሆኖም በሱ በኩል ያን ያክል የተሳካለት አልነበረም። ከ 2005-2009 ዓም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የመካኒካል ምህንድስና ትምህርቱን ተከታትሎ ጨረሰ። ለጥቂት ጊዜያት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቶ በ 2011 ዓም ደግሞ የኢትዮጵያ ማሪታይም ማሰልጠኛ ተቋምን ተቀላቅሎ አስፈላጊውን ስልጠና ካጠናቀቀ በኋላ በልጅነቱ ሲመኘው የነበረውን የመርከበኝነት ሙያ ተቀላቀለ። አሁን ንብረትነቱ የግሪክ በሆነ ድርጅት ውስጥ መሀንዲስ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። እስካሁን "ደብተራ" የሚል ርዕስ ያላት አንዲት መድብል የጻፈ ቢሆንም ለወደፊት በአጫጭርና ረጃጅም ልቦለዶች ለመምጣት ሀሳቡም ምኞቱም አለው።