
የጦርነት ጥበብ
Summary
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ከ200 በላይ ሀገራት በአንደም ይሁን በሌላ መንገድ የጦርነት ውጤቶች ስለመሆናቸው ብዙዎች ይገነዘባሉ፡፡ ከዘ-ፍጥረት ጀምሮ እስከአሁን ተፈጥሮን መሰረት ባደረገ መልኩ ድንበራቸውን ያሰመሩ፣ ግዛታቸውን ያጸኑም ሆነ ስርዓተ መንግስታቸውን ያነጹ ሀገራትን በዓለም ላይ አስሶ ማግኘት የሚቻል አይደለም፡፡ የዓለምን ታሪክ ገልጠን ባነበብን ቁጥር ከገጽ-ገጽ የሀገራት ጦርነት ታሪክ በማይነትብ የታሪክ አምድ ስር ተከትቦ እናገኘዋለን፡፡ ከዚህ ተነስተን የዓለም ሀገራት የጦርነት ውጤቶች ናቸው ለማለት ብንደፍር ያን ያህል ጥርስ የሚያስገባ ሀሳብ አይሆንም፡፡ በጦርነት ተሰርተው፣ ከጦርነት የተወለዱ ሀገራት ነጋቸው አልጋ በአልጋ ሆኖ በሰላማዊ መንገድ ዳር ድንበራቸውን አስጠብቀው ይዘልቃሉ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ የትላንት ታሪካችንን ከታሪክ መጻህፎቻችን የመጀመሪያ ምዕራፎች መረዳት የምንችል ቢሆንም ዛሬም ድረስ የጦር ነጋሪቶች፣ የሚሳኤል፣ የሮኬት ፉጨቶችና የኒውክሌየር ሙከራዎች የዓለማችን የዕለት ተዕለት ስጋቶች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍል ውስንነት፣ የህዝብ ቁጥር እያደገ መምጣት፣ የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር፣ አስከፊው የስደት ህይወት፣ የስራ ማጣት እና የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎትን ማርካት አለመቻል ዓለም ዳግም ተራምዳው ያለፈችውን አስከፊ የጦርነት ገጽታ እንድትደግመው ያስገድዳታል፡፡ ጦርነት በሀይል ብልጫ፣ በታክቲክ እና ቴክኖሎጂ ድጋፍ ከርሱ በተቃራኒው ደግሞ የተገኘውን በመውጋት ፍላጎቱን ማርካት ነውና በዚህ የጦር ቀጣና ውስጥ ከትጥቅ እና ስንቅ ባለፈ የጦርነት ጥበብን ተክኖ መገኘት አላስፈላጊ ዋጋ ከመክፈል ተርፎ አሸናፊ ሆኖ ለመዝለቅም ፋይዳው ጉልህ ነው፡፡ ይህ የጦርነት ጥበብ የሚል መጽሐፍ ለመንግስታት፣ ለጦር መሪዎች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች (መንበረ መንግስትን ተቆጣጥረው በሰለጠነ፣ በዴሞክራሲ መንገድ ምርጫን አሸንፈውም ሆነ በጉልበት ቀምተው ስልጣን ላይ መፈናጠጥ ለሚሹ) የሀገራትን ታሪክ ለሚከትቡ፣ ለፖለቲካ ተንታኝ የሚዲያ ባለሙያዎች እና በማንኛውም ወታደራዊ ሳይንስ ውስጥ ፍላጎቱ ላላቸው ሁሉ ትልቅ እውቀትን የሚሰጥ ሲሆን በአንጻሩ በየትኛውም ዘመን ለሚነሱና አሁን ላይ በስልጣን ላይ ላሉ የመንግስት አካላትም ጥሩ ምክረ ሃሳብን የሚገበዩበት እንደሚሆን ተርጓሚዎቹ ያምናሉ፡፡ ይህ መጽሐፍ ነግደው እንዲያተርፉ የሚያስችል አስተምህሮትንና ሀብት የሚያገኙበትን ምክረ ሀሳብ የሰነደ የቢዝነስ መጽሐፍ ወይም የንግድ መጽሔት አይደለም፡፡ ይልቁንም ወታደራዊ ሀይልዎን አደርጅተው፣ የውጊያ ጥበብን ተክነው በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ከሚቃጣ ጠላት ወይም በመንበረ መንግስት ላይ ስጋት በደቀነ ሀይል ላይ ድልን በመቀዳጀት እንዴት አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ጥበብን ማመላከት ነው፡፡ ስለሆነም አንብቦ መረዳትን ሳይሆን ወስዶ የመተግበርን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በወታደራዊ ሳይንስ ውስጥ ራስን ፈልጎ ለማግኘት የሚሻ ተተኪ ትውልድም ይሁን አሁን በጦር ደርጅቶ፣ በጦር መሳሪያ ሀይል መፍትሔ ለማምጣት ግድ የሚለው ሁሉ የዚህን መፅሐፍ ምክረ ሀሳብ ቢያነብብ፣ ቢተገብርም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡