የባለስልጣኖቹ ጥቅስ

የባለስልጣኖቹ ጥቅስ

Author/s: መላኩ አለም

Subjects

Politics

Published Year

2012-11-11

Book Type

Ebook

Summary

እነሆ በረከት! እነሆ መለከት ደሞ ለመመከት እነሆ ፈረሱ እነሆለት ሜዳው ሁሉም እንደህልሙ እንደጥሙ ይቅዳው! ሁሉም እንደታየው እንዳስመለከተው እንዳቅሙ ይከንዳው ሁሉም እንደመሻው…እንዲመቸው አርጎ በወግ ያሰናዳው፤ ( ሙሉጌታ ተስፋዬ) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እያለን አንድ አንዳርጌ የምንለው አብሮ አደግ ጓደኛችን አንዲት ቆንጆ ልጅ አፈቀረ፤ ነፃነት ትባላለች፡፡ ነፃነት ረጅም፣ ጠይም፣ ሎጋ፣ አይኖቿ እንደ ክዋከብት የሚያበሩ፣ ባለ ዞማ ፀጉር፣ ማንም ወጣት አይቶ በፍቅር ሊወድቅላት የሚችል የውብ ዳር የሆነች ለግላጋ ወጣት ናት፡፡ ጓደኛችን ያፈቀራት ይችን ልጅ ነው፡፡ እና ሀሳቡን ለኛ ለጓደኞቹ አካፈለን፡፡ ለቡድናችን የመጀመሪያው አፍቃሪ ነው መሰለኝ፡፡ ሲነግረን ኧረገ ምን አባቷ እንጠይቃታለን፣ አንተ ጠይቀሀት፤ እኛ ለምነናት እምቢ የምትል እሷ ማን ናት አልን፡፡ በኋላ እየዋለ እያደረ ልጅቱንም እየፈለግን ጥቂት ቀናት አለፉ፡፡ አንድ ቀን ሶስት ሆነን ስንሄድ የምትወደደው ቆንጆ ልጅ ከአንድ አቅጣጫ ብቅ አለች፡፡ ቀድሞ ያያት አፍቃሪው ጓደኛችን ነበር፡፡ ያቻትḷ አለን፡፡ ይጠበቃል ዓይን ማየት የሚፈልገውን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ ሁላችንም በአንድ አቅጣጫ ተመለከትን ግን ለምንም ነገር ዝግጁ አልነበርንም፡፡ ለካስ ያፈቀሯትን ቆንጆ ቀርቦ ለማውራት የስነ-ልቡና ዝግጅት ያስፈልግ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ዝም ብለን አወራን እንጂ ጓደኛችንም ዝም ብሎ የዓይን ፍቅር ያዘው እንጂ ምን ማድረግ እንዳለብን፣ ምን ብለን ማናገር እንዳለብን ዝግጅት አላደረግንም ነበር፤ ስለዚህ ድንገት ስትመጣ ደነገጥን፤ የምናደርገው ጠፋን፡፡ ዝም እንዳልን በፊታችን አለፈች፡፡ በዚሁ ጉዳይ ወሬ ጀመርን፡፡ እንሂድ እንከተላትና እናናግራት አለ አንደኛው ጓደኛችን፣ ሌላ ጊዜ እንጠብቅ አለ ሌላኛው፣ ዛሬ ሳይሆን ሌላ ጊዜ ከቤቷ ሂደን እናናግራታለን የሶስተኛው ሀሳብ ነበር፡፡ የሶስት ሰው ሀሳብ ተዘበራረቀ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የፍርሃት ስሜት መሆኑን ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ምክንያቱም እሷ ፈጣን ባቡር፣ ፈጣን መኪና ወይንም ነፋስ አይደለችም፡፡ ይጠበቅብን የነበረው ቢበዛ ትንሽ ሶምሶማ ሩጫ ነበር ፤ አልሆነም፡፡ ሌላም ቀን እንዲሁ በአጋጣሚ ከዚች ቆንጆ ልጅ ጋር ተገናኘን፤ አሁንም ዝም እንዳልን አለፈች፡፡ በዝምታ መተያየት ብቻ ሆነ፡፡ ሁላችንም ስለ ፍርሃታችን ከፍተኛ ደረጃ መድረስ እያሰብን ይመስለኛል፡፡ በኔ በኩል ራሴን ለስንት ነገር የምጠበቀ ጎረምሳ አደርጌ እቆጥረው ስለነበር በአንዲት የምታምር ቆንጆ ያውም የእኔ ባልሆነች ልጅ እንደዚህ ልቤ ይሸበራል ብዬ አስቤም ገምቼም አላውቅም ነበር፡፡ ግን የሆነው እንዲያ ነው። ከአንድ ጓደኛችን አንድ ሀሳብ መጣ፡፡ “ለምን ደብዳቤ አንፅፍላትም?” “Excellent idea” እንፃፍላት፤ እንፃፍላት፤ እንፃፍላት፤ ተስማማን፡፡ ማን ይፃፍ? አንተ የእጅ ፅሁፍህ ስለሚያምር አንተ ፃፍ፡፡ ሃሳቡስ? አንተ እንደሚሰማህ አድርገህ፣ አንተ እንዳፈቀርካት አድርገህ ፃፍ ተባልኩ፡፡ ተስማማሁ፡፡ ማታ ጥሩ ጥሩ የፍቅር ቃላትን አፈላልጌ፣ አገናኝቼ፣ አስማምቼ ፃፍኩት፤ ነጋ፤ ተገናኘን፡፡ ወንዝ ሂደን በዛው ሰውነታችን እየታጠብን ለማንበብ ወሰን፤ ሄድን፡፡ ወንዙ ዳር ቁጭ ብለን አነበብነው፡፡ ደብዳቤውን አደነቁት፡፡ የተጨበጨበለት ደብዳቤ ሆነ፤ በተሰብሳቢ አባላቱ ሁሉ ፀደቀ፡፡ ይሁንና አሁንም ሌላ ጥያቄ አለ፤ “ይህንን ደብዳቤ ማን ነው ወስዶ የሚሰጣት?” ገና መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው። አይን ለአይን ተያየን፡፡ አለሁ እኔ ጀግና የሚል ፓስተኛ ግን አልተገኘም፡፡ እና ምን ይሻላል? ምንም የሚሻል ነገር የለም ከመተው ውጪ፡፡ አንድ ሀሳብ ከአፍቃሪው ጓደኛችን መጣ፡፡ ደብዳቤውን የሚያደርስ ደፋር ከሌለ ሌላ ሰው አግኝቶ ከሚያነበው ወይም ደግሞ ልብሳችን ሲታጠብ ተገኝቶ ቤተሰብ ከሚያነቡትና እናንተ ዱርየዎች ከምንባል አንድ ነገር ይደረግ በሚል ውይይት ተደረገ፡፡ ከውይይቱ በኋላ ደብዳቤው ለልጅቱ የማይደርስ ከሆነ እኛ ጋ ተቀምጦ ምንም ስለማይሰራ ወንዝ ውስጥ እንዲወረወር ሀሳብ ቀረበ፡፡ ውሳኔው ፀደቀ፡፡ ደብዳቤው ወደ ወራጁ ወንዝ ተወረወረ፡፡ ወንዙ ደብዳቤውን ይዞት ጥርግ አለ፡፡ ከታች የሚዋኙና የሚታጠቡ ሌሎች አብሮ አደግ ጓደኞቻችን ደብዳቤውን አገኙት፤ አነበቡት፡፡ ከእነዚህ ጓደኞቻችን አንዱ የአፍቃሪው ጓደኛችን የክፍሉ ተማሪ ነበር፤ ከጓደኞቹ ጋር ክርክር ገጠመ፡፡ “ይህንን ደብዳቤ አንዳርጌ አልፃፈውም፤ እኔ የእጅ ፅሁፉን አውቀዋለሁ” አለ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ፤ “የራሱን ስም እያየኸው ለምን ትከራከረናለህ” ብለው ሞገቱት፡፡ ሊተማመኑ አልቻሉም፤ ደብዳቤውን ይዘውት እኛን ፍለጋ መጡ፡፡ በውሃ በበሰበሰ ረጅም ቢጫ ወረቀት ላይ የተፃፈውን ደብዳቤ አሳዩንና ማን እንደፃፈው ጠየቁን፤ ሶስታችንም ተያየንና በሳቅ ሞትን፡፡ አጋጣሚው የሚገርምና የሚያስቅ ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር በደንብ አስረዳናቸው፡፡ ደብዳቤውን አደነቁት ወደ ፊት ደራሲ ትሆናለህ አሉኝ፡፡ ደራሲ ትሆናለህ ?….።አሁን ወደ ራሴ ሀሳብ ልመለስ፤ ደራሲ መሆን እንዴት ነው? ዝም ብሎ መፃፍ ደራሲ ያደርጋል እንዴ? አያደርግም፤ ዝም ብሎ መፃፍ ደራሲ አያደርግም፡፡ታዲያ እኔ ማን ነኝ? እንጃ ! ---፡፡ በዚህ መፅሀፍ ውስጥ የተካተቱ አጫጭር ልቦለዶች ተጽፈው መፅሐፍ ለመሆን በቁ፡፡ አንድ ግሪባዮዶቭ የተባለ የሩሲያ ደራሲ አንድ ተውኔት ፅፎ ነበር፡፡ “ከማወቅ የመጣ ሀዘን” ነው ርዕሱ፤ ይህ ተውኔት በሩሲያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ ያለው ነው፡፡ ሀሳቤ ግን ከተውኔቱ ትልቅነት ላይ ሳይሆን ከርዕሱ ላይ ነው፡፡ ይህ ደራሲ ከማወቅ የመጣ ሀዘንን ሲጽፈውና ለሰው ሲያካፍለው ደስታ የተሰማው ይመስለኛል፡፡ እኔም እንደዚህ ሰው ከማወቅም ይሁን ካለማወቅ የመጣ ሀዘንን፣ ከማወቅም ይሁን ካለማወቅ የመጣ ደስታን ለአንባቢ ማድረስ ተገቢ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ ጥሩ አደረኩ አይደል? መልካም ንባብ፡፡

0.0 (0 reviews)