
አንድሮሜዳ
Summary
ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ያሉ የውጭው ዓለም ጸሐፊዎች በርካታ ጥናትና ምርምር በማድረግ “ጥንታዊ ዘሮች” (Old race) በመባል የምትታወቀው የኢትዮጵያ ግዛቷ ከሕንድ እስከ ስፔን፣ እንዲሁም በጥንታዊ የአሜሪካ ግዛቶች ሳይቀር አሻራዋ እንዳለ ጽፈዋል፡፡ በጽሑፎቻቸው ሁሉ አውሮፓና እስያ ባልሠለጠኑበት ዘመን ኢትዮጵያ ግን የቀደመ የዓለማችን ሥልጣኔ የነገሠባት ግዛት እንደነበረች በስፋት አንሥተውታል፡፡ ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ሕንፃ፣ ሒሳብ፣ ግብርና፣ ሕክምና፣ የከዋክብት ጥናት… ወዘተርፈ የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ብዙዎች አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የዚህ መጽሐፍ ዋና ዓላማ ከምርምራቸው ውስጥ የሥነ ፈለክ (የሕዋ) ዕውቀታቸውንና በዘመናት አቆጣጠር ላይ የነበራቸውን መራቀቅ ማቅረብ ነውና ያንን ድንቅ ዕውቀት በጥቂቱም ቢሆን አቅርበነዋል፡፡ የዛሬ አራት ሺሕ ዓመት ኢትዮጵያ የነበራት የሕብረ ከዋክብት ዕውቀት በስፋት አሁን ካለው የሳይንስ ግኝቶች ጋር በጣምራ አስፍረነዋል፡፡ ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን በራሳችን ቋንቋ ፕላኔቶችን ስለ መሠየማቸው፣ ስለ ስፋታቸውና መጠነ ቁሳቸውም ጭምር ሳይቀር የገለጹት በዚህ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን አሁን ያለው ትውልድም ይረዳው ዘንድ አሁን ሳይንሱ የመዘገባቸው ልኬቶችም አብረው ተጠቅሰዋል፡፡ የልኬት ልዩነቶች ቢኖሩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት የተጠቀሙበት የተለያየ ዘዴ በመሆኑ ተብሎ ሊታሰብ ይችል ይሆናል እንጂ ይህ ወይም ያኛው ስሕተት ነው ብሎ መደምደምን አሁን ያለው ሳይንስም አይደግፍም፡፡ ሳይንስም ከዓመታት በፊት ያነሣቸውን ሳይንሳዊ ሐሳቦች በዐዲስ እየተካ መሄዱ የተለመደ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በመጻሕፍታቸው ላይ ስለ ሩቅ ዓለማት፣ ስለ ከባቢ አየር፣ ስለ ደመናና መብረቅ፣ ስለ ጨረቃ፣ ስለ ፀሐይ፣ ስለ ግርዶሽ (የፀሐይና የጨረቃ) ሁሉ ሳይቀር የጻፉት በዚህ መጽሐፍ ላይ የዳሰስነው ሲሆን አሁንም ዘመናዊው ሳይንስ የደረሰበትን በትይዩ እያመሳከረ ትውልዱ እንዲመራመርበት የብራናው ፎቶ ከሳይንሱ ሥዕል ጋር በመጣመር በዚህ መጽሐፍ ላይ ቀርቧል፡፡ ከኢትዮጵያ ጥንታዊ መጻሕፍት ጋር ስለተያያዙት ስለ አራቱ ንጉሣውያን ከዋክብት፣ ስለ 12ቱ ዞዲያክ ከዋክብት፣ ስለ አራቱ ነባር ንጥረ ነገሮች፣ ስለ አራቱ ወቅቶች በእኛ መዛግብት ውስጥ የተጻፉ ዕውቀቶች አሁን ዘመናዊው ሳይንስ ከደረሰበት ግኝት ጋር በሕብረት ጽፈነዋል፡፡ ሳይንቲስቶችን አሁን ድረስ ተፈጥሮው በግልጽ ስላልታወቀው ስለ “ጨለማው ጉድጓድ” (ብላክ ሆል) በስፋት የጻፍን ሲሆን የብዙዎችን ቀልብ ስለሚስቡትና ሳይንስም ይህ ነው ብሎ እርግጠኛ ሆኖ ስለማያወራቸው “መጤ ፍጡራን” (Aliens) በኢትዮጵያ ዶክመንት ያሉትን ከሳይንሱ ጋር በማቀናጀት አቅርበነዋል፡፡ በመጨረሻም ልዩ ስለሆነው የኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከጥቃቅን የጊዜ መስፈርት ከሳድሲት ጀምረን እስከ ታላቁ የጊዜ መስፈርት እስከ 532 ዓመት ዐቢይ ቀመር ድረስ ያለውን ዳሰነዋል፤ ይልቁኑ በጣም የሚያስገርም ስለሆነው የሰባተኛው ጳጒሜን ጉዳይ ከነሒሳብ ስሌቱ ለሁሉ በሚረዳ መልኩ ቀርቧል፡፡