ሰውና ሃሳቡ
Summary
‘ሰውና ሃሳቡ’ አስ ዘ ማንቲንክዝ (As the man thinketh) የሚለው የእንግሊዛዊው ጀምስ አለን (ከ1848-1912 ዓ.ም) መጽሐፍ የአማረኛ ትርጉም መጽሐፍ ነው፡፡ አስ ዘ ማንቲንክዝ (As the man thinketh) በዓለም ዙሪያ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሠዎችን ያነቃቃና በከፊልም ሠዎች ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያሻሽሉ ከማድረግ ባለፈ በኖርማን ቪንሰንት ፒል፣ ኦርል ናይቲንጌል፣ ጄሰንዊትሌን እና በሌሎች ብዙ የዘመናችን ፀሃፊዎች ላይ አሻራውን ያሳረፈ ዘመን የማይሽረው መጽሐፍ ነው፡፡ ራሱ ጀምስ አለን ይህች ትንሽ መድብል እያለ የሚጠራት ይህች አስ ዘ ማን ቲንክዝ (As the man thinketh) የምትል መድብሉ በአምስት ታላላቅ ቋንቋዎች ተተርጉማ በሚሊዬን የሚቆጠሩ አንባቢዎች የሰው ህልም በሃሳብ ኃይል ብቻ በቀላሉ እውን ሊሆን እንደሚችል እንዲያውቁ ረድታለች፡፡ ተርጓሚው መክብብ አበበ ስለ ጀምስ አለንም ሆነ ስለ ሥራዎቹ የሚያውቀው አንድም ነገር አልነበረም፤ ይሁንና የስነ-አዕምሮ ሀኪም የሆነው ዶ/ርምህረት ደበበ በአንድ ወቅት በሸገር ካፌ ፕሮግራም ላይ በተደረገለት ቃለ መጠይቅ በስነ-ልቦና ዙሪያ ከተፃፉት መፅሐፎች መካከል መነበብ አለባቸው የምትላቸውን መጽሐፎች ጠቁመን ተብሎ ከአድማጭ ለቀረበለት ጥያቄ በአንደኝነት ያስቀመጠው አዝ ዘ ማን ቲንክዝ(as the man thinketh) የሚለውን የጀምስአለንን መፅሐፍ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ምህረት ደበበ መፅሐፉ በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደተፃፈ፣በአሁኑ ጊዜ በስነ-ልቦና ዙሪያ ለሚፃፉ ብዙ መፅሐፎች መነሻ ተደርጎ እንደሚወሰድና መፅሐፉን ከኢንተርኔት ላይ ማግኘት እንደሚቻል በሰጠው ጥቆማ መሰረት ተርጓሚው ከጀምስ አለን ሥራዎች ጋር ሊተዋወቅ ችሏል፡፡ ተርጓሚው መክብብ አበበ መፅሐፏን ደጋግሞ ካነበባት በኋላ ለሌሎች አንባቢዎች መድረስ አለባት የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሱ ይህችን ትንሽዬ ነገር ግን ለህይወት ዘመን የሚጠቅም ምክር የያዘች መፅሐፍ በክፍል አንድ ከሌላኛዎቹ የጀምስ አለን ማን ዘ ኪንግ ኦፍ ማይንድ፣ ቦዲ ኤንድ ሰርከምስታንስ (Man the king of mind, body and circumstance) እና ፍሮም ፓሽን ቱ ፒስ (From passion to peace) ከሚሉ ሁለት አነስተኛ መድብሎች ጋር እንዲሁም በክፍል ሁለት ደግሞ ላይት ኦን ላይፍስ ዲፈከልቲስ (Light on life’s Difficulties) ፣ ፋውንዴሽን ስቶንስ ቱ ሃፒነስ ኤንድ ሰክሰስ (Foundation stones to happiness and success) አውት ፍሮም ዘ ኸርት (Out from the heart) በማዳበል ሰውና ሃሣቡ በሚል ርዕስ እነሆ ብሏል፡፡ ሰውና ሃሳቡ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያገኘና አራት ጊዜ ያህል ለመታተም የበቃ መጽሐፍ ነው፡፡