ምጥን ቅመም ፭
Summary
ቅመም የምግበ ሥጋ ማጣፈጫ ነው፡፡ ከበዛ ግን ደዌ ይሆናል፡፡ ስለይኽ መመጠን ይኖርበታል፡፡ የኔዋ ቅመምም የተመጠነች ናት፡፡ ከጣራ በላይ አታስቅም፤ አዝናንታም አታዘናጋም፡፡ ግና ዘና እያደረገችና እያስፈገገች ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም መምህራነ ወንጌል፣ የተጣላን አስታራቂ ሽማግሌዎች፣ በቤተሰብ ወግ ተናጋሪዎች፣ የስብሰባ መሪዎች፣ የጽሑፍ አቅራቢዎች.....ብቻ ሁሉም የዐውድ መሪዎች በያዙት ቁም ነገር መኻል እንደ ቅመም ጣል ያደርጓትና እንደ አመቻቸው ያስፋፏት ዘንድ እነሆ! ተመጥና ቀርባለች፡፡ የመጽሐፏ አቀራረብ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ እያንዳንዱ ምሳሌ በርእስ ተከፋፍሎ የቀረበ ሲሆን በስተመጨረሻው ደግሞ የምሳሌውን ስለምንነት ለማሳየት ያህል በዚህ ምልክት (⁕⁕⁕) በመለየት የራሴን አሳብ አክዬበታለሁ፡፡ እኔ በእያንዳንዱ ወግ ማሰሪያው ላይ ለመነሻ ያህል በመጠኑ እ ንደዚያ ካልኩኝ አንባቢው የምሳሌውን ቁም ነገር ከተረዳ በኋላ ስለ ምንነቱን እንደ አመቺነቱ እየተነተነ ሊማርበትና ሊያስተምርበት ይችላል፡፡ ውድ አንባቢዎቼ ቁጥር አንድን፤ ቁጥር ሁለትን፤ ቁጥር ሦስትንና፤ ቁጥር አራትን አንብባችሁ ግልጽና ቀና የሆነ አስተያየታችሁን እንደለገሳችሁኝ ሁሉ አሁንም ይህንን ቁጥር አምስት መጽሐፌን አንብባችሁ ይጠቅማል በማለት ያሰባችሁትን ሁሉ ሳትሰስቱ በተናፋቂው አስተያየታችሁ ታደርሱኝ ዘንድ በታላቅ አክብሮትና ትሕትና እጋብዛችኋለሁ፡፡ ዲያቆን ምትኩ አበራ (B.TH.)