እችላለሁ ካልክ ትችላለህ
Summary
ችግር ሲገጥማችሁ በተለይም ችግሩ ትልቅና ፈታኝ እንዲሁም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሲሆን ሳታቋርጡ መተግበር ያለባችሁ አንድ መርሕ አለ፡፡ ፈጽሞ የያዛችሁትን አታቋርጡ፤ አታቁሙ፡፡ ማቋረጥ ሙሉ ሽንፈትን መጋበዝ ነው፡፡ ማቋረጥ ስብዕናንም በማዳከም የተሸናፊነት ሥነ-ልቡናን ያዳብራል፡፡ የምትከተሉት ዘዴ ካልሠራ ችግሩን በሌላ መንገድ ለመፍታት ሞክሩ፡፡ አዲስ የተከተላችሁት መንገድ ካልሠራ ከመፍትሔ ላይ የሚያደርሳችሁን ቁልፍ እስክታገኙ ድረስ ዘዴዎቻችሁን እየለዋወጣችሁ ሞክሩ፡፡ ሁልጊዜም ለሚገጥሙን ችግሮች ቁልፍ አለ፤ ይህ ቁልፍ ግን ሊገኝ የሚችለው ባላሳለሰ ጥረትና አስተውሎ በመፈለግ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ስኬታማ የማይሆኑት በከፊልም ቢሆን በውስጣቸው የተቀናጁ ባለመሆናቸው ነው፡፡ ማንና ምን መሆናቸውን አያስተውሉም፡፡ ብዙ ጊዜ ‹‹ሰው የራሱ ጠላት ነው›› ሲባል ሰምተናል፡፡ ሰዎች ግቦች ሲኖራቸው ፣ በርትተው ሊሠሩ ይችላሉ እንዲሁም ድካማቸውም ሁሉ መና ሊቀር ይችላል፡፡ አንድ ሰው አንድ ነገር ለማሳካት ሲመኝ ፤ ምኞቱም ሊከሽፍበት ይችላል ለምን? ምናልባት ችግሩ ከውስጡ ይሆናል፡፡ በመሠረቱ በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ ለማወቅ የሚያስቸግረው ራስን ማወቅ ነው፡፡ ሁልጊዜም የምንፈልገውን ለማድረግ የሚሞክር አብሮን የተሠራ ራሳችንን መጠበቂያ ዘዴ አለን፡፡ ይህ ሥርዓት ያለማስተዋል የተሠራውን በብልኀት እንደተሠራ ለማስመሰል ይሞክራል፡፡ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ለማወቅ አይፈልጉም፡፡ ስለ ሌሎች ሰዎችና ችግሮቻቸው ያወራሉ ነገር ግን ከእውነታ ጋር ላለመጋፈጥ ከራሳቸው ይደበቃሉ፡፡ በርግጥም አንድ ሰው በእድገት ኺደቱ ከሚደርስባቸው ከፍተኛ ደረጃዎች አንዱ መሸሸግ የማይሞክርበትና ትክክለኛ ማንነቱን ለማወቅ የሚወስንበት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መነሣሣት የሚመጣው ከባድ ችግሮችን ተመስሎ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ተሞክሮዎችን ትጋፈጣላችሁ፡፡ ይህ አንዳንዶችን ግንባራቸውን እንዲያጥፉና እጃቸውን እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ለሌሎች ግን ችግር ትልቅ ሐሳብ እንዲወጥኑና ጠንክረው እንዲሠሩ የሚያነሣሣቸው ነው፡፡ ዊልያም ኤ ዋርድ ፣ ‹‹ችግር አንዳንዶችን ይሰብራል ፤ ሌሎችን ደግሞ ክብረ ወሰን እንዲሰብሩ ያደርጋል›› ሲል ግሩም አድርጐ ገልጾታል፡፡ ምናልባት ጠቢቡ ሼክስፒይር ‹‹የመከራ ፍሬዎች ጣፋጭ ናቸው›› ያለን ለዚህ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መከራ ብርቱዎችን ወደላይ ከፍ የሚያደርግ አነሣሽ ኃይል መሆኑን ያውቅ ነበርና፡፡ ብቁ እንዳልሆኑ የማሰብን ያህል የሰውን ልጅ ሽባ የሚያደርግና በጣም መጥፎ ስሜት የሚፈጥር ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል በዚህ ችግር ስትሠቃዩ የቆያችሁ ብትሆኑ ልትገላገሉት ትችላላችሁ፡፡ ፈውሱ የሚጀምረው ለመለወጥ እንደምትፈልጉ ስትወስኑ ነው፡፡ እስካልሞከራችሁ ድረስ ምን ለማድረግ እንደምትችሉ አታውቁም፡፡ በቁርጠኛነት ወደፊት መጔዝ ከቀጠላችሁ ፣ እንደሚሳካላችሁ በማመን ከሞከራችሁ ፈጽሞ አትወድቁም፡፡ ደራሲ፡ ኖርማን ቪንሰንት ፒል ትርጉም፡ ሱራፍኤል ግርማ