ጀግና
Summary
አሁን ከምትገኝበት የኑሮ ደረጃ አንስቶ በባለጠግነት፣ጤንነት፣ስኬትና ደስታ ወደተሞላ ኑሮ የሚያደርስህ አንዳች ዓይነት ተዐምራዊ መመሪያ በኖረ ብለህ ተመኝተህ ታውቃለህ? ግቦችህን እንዴት እንደምታሳካ፣መሰናክሎችን እንዴት እንደምታልፋቸው፣ ፈተናዎችን እንዴት እንደምትወጣቸው፣ “አትችልም” የሚሉህን ኹሉ በአሸናፊነትህ እንደምትረታቸው፤ ለዚህም የሚያስፈልጉህ ብቃቶችና ጥበቦች ከወዴት እንደምታገኛቸው የሚጠቁምህን ዶሴ በጽኑ ስትፈልግ ኖረሃል? እነሆ የልብህ መሻት ዕውን ሊሆን ነው፡፡ ወደ ታላቅነት የሚያደርስህ መመሪያ ይኸውና! ምስጢሩ(The Secret) የተሰኘውን መጽሐፍና ጥናታዊ ፊልም ለዓለም የገለጠችው ርሆንዳ ባይርን አሁን ደግሞ ጀግና(Hero) የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አበቃች፡፡ እያንዳንዳችን ወደዚህች ምድር የመጣነው በየራሳችን መንገድ ራሳችንንና ዓለምን የማበልጸግ ዓላማ ይዘን ነው የሚለው ይህ መጽሐፍ አንተም ልዩ ነህና ለስኬት ተዘጋጅ ይልሃል፡፡ *** በጀግንነት ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙህ እንቅፋቶችና ፈተናዎች በሙሉ ሕልምህን ለማሳካት የሚያስችልህን ብቃትና አቅም እንድትላበስ የሚያስችሉህ ናቸው፡፡ እንዲያውም ከፍ ያሉ እንቅፋቶችና ከበድ ያሉ ፈተናዎች ባጋጠሙህ ጊዜ ሕልምህን ወደማሳካቱ እየተጠጋህ ለመሆኑ ምልክቶችህ ናቸው፡፡ *** በርካቶች ሕልማቸውን ከማሳካት የሚያግዳቸው ከመነሻው አንስቶ እስከመጨረሻው ስኬታቸው በምን መንገድ እንደሚጓዝ አስቀድመው ማየት አለመቻላቸው ነው፡፡ መቼም ቢሆን የትኛውም ስኬታማ የዓለማችን ሰው ሕልሙ በምን መንገድ እንደሚሳካ አስቀድሞ ያወቀ የለም፤አይኖርምም፡፡ አስቀድመህ ልታውቅ የምትችለው እስከሚቀጥለው መታጠፊያ ያለውን መንገድ ብቻ ነው፡፡ መታጠፊያው ጋ ካልደረስክ ቀጣዩን መንገድ ልታየው አትችልም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሕልምህ እንደሚሳካ አምነህ መንገድህን መቀጠልህ ላይ ነው፡፡ *** ስኬት መመሪያ አለው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ልምዳቸውን የሚያካፍሉን አሥራ ሁለት እጅግ ስኬታማ ሰዎች መመሪያውን ተከትለው ለስኬት የበቁ ናቸው፡፡ አሁን መመሪያውን የመከተል ተራው የአንተ ነው!