የይቅርታ መስኮት

የይቅርታ መስኮት

Author/s: እመቤት መንግስቴ

Subjects

Fiction

Published Year

2009 ዓ.ም

Book Type

Audio

Summary

‹‹የይቅርታ መስኮት›› ስሜትን ቆንጥጦ የመያዝ አቅም ያለው፣ ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ልቦለድ ነው፡፡ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ የሚገጥመው ውጣውረድ፣ ከፍታና ዝቅታ ለስለስ ብሎ በሚጓዝ የታሪክ ፍሰት ተገልፆበታል፡፡ በ140 ገፆች የተሰነደው ይህ ልቦለድ ከምንም በላይ የህይወትን ጉዞ ባልተወሳሰበና ባልተደረተ መልኩ ቀለል አድርጎ ማቅረብ እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡ ደራሲዋ እመቤት መንግስቴ ታሪኩን ያቀረበችበት ቀላልና ውብ ቋንቋ ከትረካው ፍሰት ሳንናጠብ፣ ከተመስጧችን ሳንወጣ ትኩረታችን በመፅሃፉ ገፆች መካከል እንደተሰበሰበ እንዲቆይ የሚያደርግ ኃይልን ተላብሷል፡፡ በዋናዋ ገፀ ባህሪ ተራኪነት የሚቀርበው የፍቅር ታሪክ በውስጡ ያካተታቸው ገፀ ባህሪያት ውሱን ቁጥር ያላቸው መሆኑም ታሪኩ ያለአንዳች መደነቃቀፍና ግርታ ወደ ልባችን ሰተት ብሎ እንዲገባ ያስቻለ አንዱ ገፅታው ነው፡፡ የዚህ ልቦለድ መፅሃፍ አስኳል የሰው ልጅ ህይወት ታላቅ ሚስጥር፣ የስኬቱም ሆነ የውድቀቱ ማጠንጠኛ፣ የደስታውና ኃዘኑ መነሻና መድረሻ፣ የህይወት ጣዕም መገለጫ የሆነው ፍቅር ነው፡፡ የፍቅር ጥምረት ስለ ህይወት፣ ስለ ዓለም፣ ስለ ሰው ልጅና ስለኑሮ ያለንን ዕይታና አመለካከትን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ በመቅረፅ ረገድ ያለው ድርሻ በልቦለድ ታሪኩ ውስጥ እጅግ መሳጭ በሆነ መልኩ ተገልጿል፡፡ የሰው ልጅ ከሚያስተናግዳቸው ስሜቶች ሁሉ ፍቅር በእጅጉ ይልቃል፡፡ ኃዘኑም ሆነ ደስታው በፍቅር ይቃኛል፤ ንዴቱም ሆነ ብስጭቱ በፍቅር ይበርዳል፤ በውስጡ የያዘው ቂም፣ ጥላቻና በቀልም በፍቅር ይሽራል፡፡ የሰው ልጅ ሊኖረው የሚችለው የትኛውም ዓይነት ባህሪ፣ ፀባይና ስሜት ሁሉ ከፍቅር በታች ናቸው፡፡ ‹‹የይቅርታ መስኮት›› ልቦለድ መፅሃፍ የፍቅርን ይቅር ባይነት ጥግ በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ... ምናልባትም ከምንገምተውና ከምናልመው በላይ በገሃድ እንደሚገለጥ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡ በየዕለቱ የምንጠራው ይቅርታ የበሽታዎች ሁሉ ፈውስ፣ የችግሮች ሁሉ መፍቻ መሆኑን ከ ‹‹ የይቅርታ መስኮት ›› በላይ ማስረጃ የለም፡፡ እመቤት መንግስቴ ቀደም ሲልም ሌሎች ስድስት መፅሀፍትን ለንባብ አብቅታለች፡፡ ሲያሻት በግጥም ሲስፈልጋት በስድ ንባብ እየተመላለሰች የሥነ-ፅሁፍ አቅሟን አሳይታናለች፡፡ እመቤት አሜሪካን አገር የምትኖረው ከኢትዮጵያዊ ባህልና ትዝታዎቿ ጋር ነው፡፡ የዚያን አገር የኑሮ ዘይቤና የህይወት መንገድ ስትጨምርበት ደግሞ የዕይታ አድማሷን ገደብ የለሽ አድርጎላታል፡፡ ይሄም በ‹‹የይቅርታ መስኮት›› ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ ‹‹ሀበሻ ነሽ?..›› በሚል ተራ ትውውቅ የተጀመረውን ግንኙነት ሰማይ ቤት ቀጠሮ ድረስ ወስዳ አስደምማናለች፡፡ የገፀባህሪያቱ የፍቅርና የህይወት ውጥንቅጥ የራሳችን መስሎ እንዲሰማን ፣ ደስታና ሀዘናቸውን እንድንጋራ በማድረግ የብዕሯን ጉልበት አሳይታበታለች፡፡ ሞገስ ሃብቱ

0.0 (0 reviews)