ከሌብነት ወደባልነት
Summary
‹‹ምኞቴ የፈጣሪ የጥበብ ዜማ በውስጤ የሚንቆረቆርብኝ ወርቃማ ዋሽንት መሆን ነው።ከዋሽንቱ የሚወጣው የእግዚያብሄር ህልውና ያረፈበት ዜማ እያንዳንድን የአዳም ልጅ ልብ በመሰርሰር ወደልቡ ሰርጎ እንዲገባና የተስፍና የመፅናናት መንፈስ እንዲበተንበት የማድረግ አቅም እንዲኖረው እፈልጋለሁ….እኔ የንብረታቸውን ልክ ከማያውቁ ሰዎች በመስረቅ ለሚስኪን ወገኖቹ የእለት ሳቃቸውን የምለግሳቸውና የማታ ጉርሳቸውን የምሸምትላቸው እርበኛ ነኝ።››.. ይሄ ዋናው ገፀ-ባህሪ እንደህይወት መመሪያው ሚገለገልበት መሪ ቃሉ ነው፡፡ በህይወት አስፈላጊው ነገር እያለቀስን ብንወለድም …ፈገግ ብለን ኖረን …እየሳቅን መሞት መቻላችን ነው፡፡እንደዛ ካደረግን ስለህይወት የሆነ ነገር ገብቶናል ማለት ነው፡፡እና በዚህ የህይወት ጉዞችን ጥበበኞች መሆን አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ጥበብ ማለት ደግሞ በጥልቅ ትኩረት ግን ደግሞ በጥቂት ልፍት ከአጋጣሚዎች የመጨረሻውን ውበት በማውጣት የተሻለ የተባለ ጥቅም ማግኘት ማለት ነው። በዚህ ልብ-ወለድ ውስጥም የምናየው ይሄንኑ ነው፡፡….ለዘመናት ከተሰማራበት የሌብነት ስራ በአጋጣሚ ላገኛት ወጣት እጅ በመስጠት በፍቅር መሰላልነት ተንጣለጥሎ ወደ ባልነት የተሸጋገረበትን ውጣ ውረድ የተሞላበትን ታሪክ የሚያትት መፅሀፍ ነው፡፡፡ አንዳንዴ ሲኦል ውስጥ ተጥለን እዛ እየዳከርን ቢሆንም በሆነ ቅፅበታዊ አጋጣሚ ወደገነት የሚያስፈነጥረንን ወርቃማ መሰላል የማግኘት እድልና አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ያንን ያገኘነውን እድል ደግሞ በጥበብ የመጠቀም ብልሀት ከእኛ እንደሚጠበቅ ጥቆማ የሚሰጥና በህይወትም ተስፋ የሚሰጠን መሰረቱን ፍቅር ላይ ያደረገ የህይወት ውጣ ውረድን የሚያሳይ ልብ አንጠልጣይ በአንደኛ መደብ (በትረካ) መልክ የቀረበ ወጥ ልብ-ወለድ ነው፡፡ ‹‹ከሌብነት ወደ ባልነት›› መፅሀፍን ፈቅዳችሁ ለማንበብ ከወሰናችሁ ትወዱታላችሁ ብዬ እተማመናለሁ፡፡ መልካም ንባብ!! ደራሲው