ብዕረኛው የሞጃ ልጅ
Summary
በዚህ ስብስብ በመጀመሪያ ያለው የወንበር ላይ ጉብኝት ሲሆን ይህም ሩቅ ሳይሄዱ ባሉበት ሆነው በምናብ የሚጎበኙበትና ‹አርም ቼር ቱሪዝም› የሚሉት ነው፡፡ በኔ ዓይን የማሳያችሁ በተለያዩ ወቅቶች ያየኋቸው ስፍራዎች አሉ፡፡ እንጓዝ እያልኩ ስለምንና መጓዝ ብዙም ባልተለመደበት በሰሜን ሸዋ ጉዞን በፍላጎቴ ሳስተባብር ያለፍኩበትን ታያላችሁ፡፡ ለረጅም ዓመታት ማለትም እስከ 2006 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከ200 ኪሎሜትር ርቀት በላይ ተጉዤ እንዳለማወቄ የጉዞው ምዕራፍ ተከፍቶልኝ እያንዳንዷንም እየጻፍኩ ሰውን ለማጓጓት መቻሌ ለራሴ ይገርመኛል፡፡ ከቤቱ ሃያ ኪሎሜትር የሚርቀውን ‹‹ሰላድንጋይን በ30 ዓመቴ አየሁት›› ካለው ከሰፈሩ ወጥቶ ከማያውቀው አጎቴ አደናውሰኝ ዘነበ አልለይም ነበር፡፡ በተለይ ከጉዞ አንጻር መማርም ሆነ ስራ መያዝ የማይለውጠን ነገር ይደንቀኛል በእውነቱ! ስንቱ ነው አራት ወይም አምስት ልጅ ስለወለደ ብቻ ዓለሜን ቀጨሁ ብሎ የሚኩራራው! ዓለሚቱን አግብቶ ይሆናል እንጂ ዓለምማ ሰፊና በምናቡም በላይ ነች፡፡ ቢያንስ ሰባቱን የዓለም አስደናቂ ቦታዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብዙ የሚቀሩንና አይተናቸው ልናደንቃቸውና እንደ አርአያ ልንወስዳቸው የሚገቡን ስፍራዎች አሉ - 187 አገሮችን እንደጎበኘው ያገራችን ልጅ ፍቅሩ ኪዳኔም ባይሆን የተወሰኑትን ለማየት ማቀድ ይኖርብናል፡፡ ለጉብኝት ዓላማ ብዬ ከሄድኩባቸው ቦታዎች በዘለለ በስራ አጋጣሚ የሄድኩባቸውንም አስቃኛችኋለሁ፡፡ በየሄድኩበት ማስታወሻ እይዝ ስለነበረ የተጓዝኩበትን ሁሉ ትጎበኛላችሁ፡፡ በሁለተኛው ክፍል የማቀርባቸው ጽሑፎች በንባብ ላይ ስለሰራኋቸውና ሌሎች የማህበረሰባዊ ለውጥ ስራዎች ናቸው፡፡ በንባብ ላይ ነው ሲባል በዚያ ውስጥ ታሪኮች አሉ፡፡ ሰዎች አሉ፡፡ ደረቅ ሪፖርት አይደለም፡፡ በንባብ ላይ ስሰራ ህብረተሰቡን ካስነበብኩባቸው መንገዶች የተወሰኑትን ላስቃኝዎት፡፡