የውህዳን ምድር
Summary
ኦሮሞዎች ወለቃን ለመውጋት መጡ። የኦሮሞዎችም መሪ የያኔው ምርኮኛ ያሁኑ ተሳዳጅ የሱስንዮስ አሳዳጊና ወዳጁ ቡኮ የተባለው ሰው ነበረ ። በወቅቱ የሆነውን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከንጉሥ ሱስንዮስ ለታሪክ ቀድተው ካሳፈሩልን እንመልከት ። ሱስንዮስ ለመንገስ ባመፀበት ጊዜ ኦሮሞዎች ወለቃን ለመውጋት መጡ። አባይ አጠገብ ጽጃ በር ከምትባል አምቦ (ሐራ) ሲደርሱ ኦሮሞዎች አዩአቸው። ኦሮሞዎች ሰው እንዳለ ሲያዩ ይሄ ማነው ብሎ መሪያቸው ከፍ ባለ ድምፅ ተጣራ ። ሱስንዮስ ነው አሉት ። ይሄን ሲያውቅ የንጉሡ ልጅ ወዳለበት ሰደይ ወደ ምትባል ወንዝ ደረሰና እግሮቹ ላይ ወደቀ ። የእግሮቹን ጣቶች እየጠባ በፍቅር እንጉርጉሮ አንጎራጎረ ። እጅግ ወደቀለት። የዚህ ኦሮሞ ስም ቡኮ ነው ። ከኮኖ ነገድ ። ሰደይ ወንዝ የሱስንዮስ እና የአሳዳጊ አባቱ የቡኮ ዳግም መገናኛና ናፍቆት መውጫ ብቻ አልነበረችም ። ይልቁንም ከሰደይ ወንዝ ዳግም ግንኙነቻው ጀምሮ እስከ ፍፃሜው በጋራ የሄዱበትን መንገድ ዱካቸውን ተከትለን ስናጤነውና የመጨረሻ መዳረሻ ውጤታቸውን ስንቃኝ ከዚህም ተነስተን ስንመረምር በሱስንዮስና በቡኮ እንዲሁም በወገኖቻቸው መካከል እንደ አዲስ የአብሮነት ቃልኪዳን የተገባባት መነሻ ስፍራ ናት ማለት ይቻላል ። ስለዚህ የቀደመ ፍቅራቸውን የናፍቆትና የመላቀሳቸውን እውነታ እና ቀጣይ የኑሮ መንገዳቸውን ይዘን ስንነሳ ቢያንስ ቡኮ ሱስንዮስን (ያኢልማኮ )ልጄ ወዳጄ ምን ሆንክብኝ ሲለው ሱስንዮስም ቢሆን ዘመድ ወገን ያልኳቸው አሳደዱኝ ተገፋሁ ተከፋሁ ማለቱን ቡኮም በምላሹ አይዞህ ልጄ ቤተሰብነታችን ለመቼ ነው እኛ አለንልህ ። እስከመጨረሻው ሞት እንኳን ቢሆን በክፉም በደጉም አብረን እንሆናለን እንዳለው እናስባለን ። በሰደይ ወንዝ በሱስንዮስና በቡኮ እንዲሁም በሁለቱም ወገኖች መካከል ቀድሞ የነበረው እንዳለ ሆኖ የአዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ጅማሮ ችቦ ተለኮሰ ። የሱስንዮስና የቡኮም ልጆች የአብሮነት ቃል ማሰሪያ ስፍራ መሆኗን የሚገልጽና የሚያጎላ የፍቅርና የህብረት ሀውልት ሊቆያቆሙባት ይገባ ነበር ። ከመፅሐፍ የተወሰደ